የሀገር ውስጥ ዜና

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

By Meseret Awoke

August 19, 2020

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ13፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ከተከናወነ በኋላ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ለግንባታው የሚውል ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ከግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በኋላ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።

ከሙሌቱ በኋላ በአንድ ወር ጊዜ ወስጥ ብቻ ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ለግንባታው ድጋፍ መሰብሰቡን የፅህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም ተናግረዋል።

ለግድቡ ግንባታ ስኬት የመንግስትና የግል ተቋማት፣ ባንኮችና ኢንሹራንሶች፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብ እንደ አጠቃላይ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ዳግም ከፍተኛ መነቃቃት እያሳዩ መሆኑንም ነው የተናሩት።

ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ ከ8100 “A” አጭር የፅሁፍ መልእክት ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ11 ሚሊየን 271 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በዚሁ ወር ከቦንድ ግዢ እና ከስጦታ ደግሞ 105 ሚሊየን 201 ሺህ 874 ብር መሰብሰቡን አቶ ሃይሉ ገልጸዋል።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለግድቡ የተደረገው ከእስካሁኖቹ ከፍተኛው መሆኑንም ነው የገለጹት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ 13 ቢሊየን 800 ሚሊየን ብር ከህዝብ መሰብሰቡን ኢዜአ ዘግቧል።