አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጆርጂያ በተከሰተው የቱርክ ወታደራዊ አውሮፕላን መከስከስ አደጋ 20 ወታደሮች እና የበረራ አባላት ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
የቱርክ አየር ኃይል ንብረት የሆነውና ሲ-130 የሚል ስያሜ ያለው ወታደራዊ አውሮፕላኑ ከአዘርባጃን ተነስቶ ወደ ቱርክ እየበረረ በነበረበት ወቅት ነው በጆርጂያ ሲግናጊ ማዘጋጃ ቤት አካባቢ የተከሰከሰው።
የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት የአውሮፕላኑ በረራ ተዛብቶ ወደ መሬት ሲወደቅ ታይቷል፡፡
ትናንት ጠዋት ከቱርኳ ትራብዞን ከተማ ተነስቶ ለወታደራዊ ተልዕኮ ወደ አዘርባጃኗ ጋንጃ ከተማ የተጓዘው አውሮፕላኑ÷ ከጋንጃ ከተማ ወደ ቱርክ እየተመለሰ በነበረበት ወቅት ለ27 ደቂቃ ከራዳር በመሰወር ከደቂቃዎች በኋላ በጆርጂያና አዘርባጃን ድንብር አቅራቢያ መከስከሱን ኤን ቲቪን ጠቅሶ አር ቲ ዘግቧል።
የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 20 ወታደሮች እና የበረራ አባላት በአደጋው ህይወታቸው አልፏል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶኻን ከጆርጂያ ባለስልጣናት ጋር በመቀናጀት የአውሮፕላኑን ፍርስራሾች የማስመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው÷ የአደጋው ምክንያት እየተጣራ ይገኛል ማለታቸውን አር ቲ እና አልጀዚራ ዘግበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ