አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሚዛናዊነት የጎደላቸው የጅምላ ፍርድ እና በልጥፎች ስር የሚሰጡ አስተያየቶች ብዙዎችን ለከፍተኛ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ይዳርጋሉ። አንዳንዶች የሚወዱትንም ሥራ እስከመተው ይደርሳሉ።
በማህበራዊ ሚዲያ በግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ከእውነት የራቁ እና ክብረ ነክ መረጃዎች ይሰራጫሉ።
አንዳንድ መጥፎ እና ከልጥፉ ይዘት ጋር የማይገናኝ አስተያየት የሚሰጡ ተጠቃሚዎች ደግሞ በመህበራዊ ሚዲያ አድራሻቸው ላይ ስለራሳቸው የሚገልጽ ምንም መረጃ የላቸውም።
ፋና ፖድካስት ይህንን ጉዳይ ከስነ ልቦና እና ሕግ አንጻር እንዴት እንደሚታይ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
የሥነ ልቦና ባለሙያ ትዝታ አየለ እንዳሉት÷ ማንነታቸውን ደብቀው በማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ስር አሉታዊ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ከሥነ ልቦና አንጻር ራሳቸውን የሚወዱ፣ ጥቅም ፈላጊ ወይም ደግሞ በራስ መተማመን የሌላቸው ናቸው።
እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እውነተኛ ማንነታቸው እና የሚያደርጉት ተግባር የተጋጨባቸው መሆኑን በመጥቀስ÷ ውስጣዊ ሰላም የሌላቸው፣ ከአዕምሮ ጤንነት ወይም ከአስተዳደግ ጋር በተገናኘ የአዕምሮ ጠባሳ ያለባቸው እንደሆኑም አንስተዋል።
ከሥነ ልቦና ጋር በተገናኘ ሊሸፍኑት የሚፈልጉት አንዳች ነገር እንዳለም የሚገልጹት ባለሙያዋ÷ ስለዚህም በግልጽ ወጥተው ሃሳባቸውን መግለጽ አይችሉም ነው ያሉት።
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማንነታቸውን ሳይገልጹ ድብቅ በሆነ መልኩ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያሰራጩ እና አስተያየት የሚሰጡ አካላት እንዲሁም የጅምላ ፍርድ በሰዎች የዕለት ዕለት ውሳኔ ላይ የራሳቸው ስነ ልቦናዊ ጫና እንደሚያሳድሩም አንስተዋል።
ማህበራዊ ሚዲያው ላይ አንድ አጀንዳ ሲነሳ በሌላኛው ወገን በኩል ያለውን ችላ በማለት የጅምላ ፍርድ ይታያል የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ትዝታ አየለ÷ በጅምላ መጓዝ እና በስሜት መረጃዎችን በማሰራጨት አጀንዳውን ማራገብ እንደሚስተዋል ይህም ትልቅ ሥነ ልቦናዊ ችግር ነው ብለዋል።
እነዚህ ሰዎች አመዛዝኖ መረጃዎችን ማየት እና መወሰን፣ ለሌሎች ማሰብና ሌሎች ላይ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን እንደማያገናዝቡም አመላክተዋል።
የሕግ ባለሙያዋ ሰብላ አሰፋ በበኩላቸው÷ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የወንጀል ተጠያቂነትን በመፍራት ራሳቸውን ደብቀው ሀሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን እንደሚያሰራጩ ገልጸዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል የሚያስችል ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዳሉም ተናግረዋል።
ስርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም አዋጅ ቁጥር 1185/2012 እንዲወጣ መደረጉን አመላክተው÷ በማህበራዊ ሚዲያ ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው ተጠቃሚ የጥላቻ ንግግር ቢፈጸም ከ2 እስከ 5 ዓመታት እንደሚያስቀጣ አስረድተዋል።
የጥላቻ ንግግር ሲባል አልፎ አልፎ የሚፈጸም ሳይሆን በየቀኑ በስፋት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምናየው ነው ያሉት የህግ ባለሙያዋ÷ የጥላቻ ንግግር ተፈጽሞብኛል የሚል አካልም ክስ መስርቶ እስከ 300 ሺህ ብር ካሳ ሊያገኝ እንደሚችል አብራርተዋል።
በብርሃኑ አበራ
ባለሙያዎቹ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇https://www.youtube.com/watch?v=9JJ4QLFRBJg