አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጭው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ዴሞክራቶችን በመወከል የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተፎካካሪ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ባይደን ፓርቲው ባካሄደው ታላቅ ጉባኤ ላይ በተካሄደው ምርጫ በይፋ የፓርቲው ተወካይ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጉባኤው ላይ የቀድሞዎቹ ዴሞክራት ፕሬዚዳንቶች ጂሚ ካርተር እና ቢል ክሊንተን እንዲሁም ሪፐብሊካኑ የቀድሞው የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፓወል ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ወቅት የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶችም ሆኑ ሪፐብሊካኑ ኮሊን ፓወል ለ77 አመቱ አዛውንት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ትራምፕ በነጩ ቤተ መንግስት “ቀውስ ፈጥረዋል” ሲሉ ወርፈዋቸዋል፡፡
ጆ ባይደን እስካሁን ከህዝብ በተሰበሰበ የቅድመ አስተያየት ትንበያ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን በተወሰነ የድምጽ ልዩነት እየመሯቸው መሆኑ ይነገራል፡፡
አዛውንቱ እጩ ዴሞክራቶችን ወክሎ ለመቅረብ ተደርጎ በነበረበው የመጀመሪያ ምርጫ ላይ በበርኒ ሳንደርስ እየተመሩ ነበር፤ ይሁን እንጅ ዘግየት ብለው በምርጫው የተሻለ በማስመዝገብ ፓርቲውን መወከል ችለዋል፡፡
ባይደን ከዚህ ቀደም በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን በምክትልነት ያገለገሉ ሲሆን በፈረንጆቹ 1988 እና 2008 ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ለመግባት በተፎካካሪነት ቀርበው ነበር፡፡
በፓርቲው ታላቅ ጉባኤ ላይ በ50ዎቹ ግዛቶች በቀጥታ ኢንተርኔት ድምጽ ተሰጥቷል፡፡
ምንጭ፣ ቢቢሲ