አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ወሳኝ ሪፎርም በማከናወን በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ቀጣና ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን ሚናዋን እየተወጣች ነው አሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ።
3ኛው የኢጋድ ሀገራት ፎረም “ሰላምና ደህንነትን ለማጠናከር የብሔራዊ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ኢጋድ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከራሷ አልፎ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ማስፈን የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም ማድረጓን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ የሰላም ኖቤል ሽልማት ማግኘታቸውን አስታውሰው ÷ በዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ሰላም የዘላቂ ተቋማት ውጤት መሆኑን ያስረዱት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር ÷÷ የለውጡ መንግስት በጸጥታ አካላት፣ በሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በፍትሕ አካላትና በሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ሪፎርም አድርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ አባል ሀገር የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና መወጣቷን አብራርተዋል።
ብዝሃ የዴሞክራሲ ተቋማትን በማሻሻልና አዳዲስ ተቋማትን በመፍጠር እውቀት መር የመንግስት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባቱን አንስተዋል።
ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ሥርዓት ማንበር፣ ተጠያቂነት ያለበት የጸጥታና ደህንነት መገንባት፣ ሙስናን መከላከል የሚያስችሉ ተቋማት ተገንብተዋል ነው ያሉት፡፡
ይሄውም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ በበኩላቸው÷ የኢጋድ ቀጣና እንደ ሽብርተኝነት፣ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና በርካታ ፈተናዎች ያሉበት መሆኑን ተናግረዋል።
ዴሞክራሲ ዜጎች በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፖለቲካ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍ ያለ ዋጋ አለው ብለዋል።
ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ፣ የሲቪል ማህበራትን ተሳትፎ ማጠናከር አካታች የግጭት አፈታት ሥርዓትን ማስፈንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመው÷ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ÷ የኢጋድ ቀጣና የጸጥታ ጉዳይ ተለዋዋጭ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ወሳኝ ነው ፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና መሰል የዴሞክራሲ ተቋማትን እያጠናከረች ትገኛለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከዚህም ባሻገር በኢጋድ ቀጣና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሀገራት የተቋማትን አቅም ማጠናከር እንዳለባችው ታምናለች ነው ያሉት፡፡