አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ወደብ ማግኘት ካልቻለች በየዓመቱ በአማካይ 50 ቢሊየን ዶላር ታጣለች አሉ የኢኮኖሚ ልማትና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ደረጀ ደጀኔ።
አማካሪው ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት እየታየበት ነው።
በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ዓመታዊ ጥቅል ምርቷ 1 ትሪሊየን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል ይገመታል ያሉት አቶ ደረጀ÷ የወጪና ገቢ ንግዱ ደግሞ የዚህን 50 በመቶ ድርሻ እንደሚሸፍን አመላክተዋል፡፡
አሁን ከወደብና ወደብ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው ላሉ ወጪዎች እያወጣን ያለነው የውጪና ገቢ ንግዱን 10 በመቶ እንደሆነ አንስተዋል።
በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ይህ የክፍያ መጠን ምንም ሳይጨምር ቢቆይ እንኳን ኢትዮጵያ በዓመት 50 ቢሊየን ዶላር ታጣለች ነው ያሉት።
ይህም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ 10 ግድቦችን መገንባት የሚያስችል ሀብት በየዓመቱ እንድናጣ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በቀጣይ ዓመታት የባሕር በር የማናገኝ ከሆነ የሀገርን ሀብት ባሕር ላይ ወርውሮ እንደመመለስ ነው ሲሉም ባሕር በር የማግኘትን ጥቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሄኖክ በቀለ
የኢኮኖሚ ልማትና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ደረጀ ደጀኔ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇https://www.youtube.com/watch?v=dVGNGN5y9i0