ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቱርክ C-130 ዕቃ ጫኝ ወታደራዊ አውሮፕላኖቿን ከበረራ አገደች

By Yonas Getnet

November 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጆርጂያ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ ቱርክ C-130 ዕቃ ጫኝ ወታደራዊ አውሮፕላኖቿን ከበረራ አግዳለች።

የቱርክ አየር ኃይል ንብረት የሆነው C-130 ዕቃ ጫኝ ወታደራዊ አውሮፕላን ትናንት ከአዘርባጃን ተነስቶ ወደ ቱርክ በረራ በሚያደርግበት ወቅት ተከስክሶ የ20 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል።

የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶኻን በወቅቱ የአውሮፕላኑን ፍርስራሾች የማስመለስ እና የአደጋውን ምክንያት የማጣራት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸው ነበር።

በዚህም ቱርክ C-130 ዕቃ ጫኝ ወታደራዊ አውሮፕላኖቿን ሙሉ በሙሉ ከበረራ ማገዷን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አሳውቋል።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው ከአደጋው በኋላ ሌሎች C¬-130 አውሮፕላኖች የቴክኒክ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

በውስጡ የሰው ኃይል እና የአውሮፕላን ጥገና አቅርቦቶችን ጭኖ ከምዕራብ አዘርባጃን በመነሳት ወደ ምስራቅ ጆርጂያ ከተሻገረ ብዙም ሳይቆይ የወደቀው አውሮፕላን፤ የአደጋ መንስኤው እስካሁን አልታወቀም።

የአደጋውን መንስኤ የሚያጣራ የምርመራ ቡድን የሚደርስበት ውጤት እንደሚገለጽ ያመለከተው ሚኒስቴሩ፤ መርማሪዎቹ ወደ አንካራ የመጡ የበረራ መረጃ እና የድምጽ መቅረጫዎችን በመመርመር ላይ መሆናቸውን አብራርቷል።

የወታደራዊ አውሮፕላኖች ዝርዝር የቴክኒክ እና የደህንነት ፍተሻዎችን አድርገው ካጠናቀቁ በኋላ እንደሚመለሱም ሚኒስቴሩ በመግለጫ ጠቁሟል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!