ቢዝነስ

በመዲናዋ ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው

By Adimasu Aragawu

November 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድ ለመከላከል እየተሰራ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን።

በከተማዋ እየተባባሰ በመጣው ሕገ ወጥ እርድ፣ የስጋና የእንስሳት ዝውውር ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ አዲስ አበባን ምቹና ለኑሮ ተስማሚ እንድትሆን የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የመዲናዋን ልማትና ውበት ለማጠናከርም በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በሕገ ወጥ እርድ፣ መሬት ወረራ፣ ሕገ ወጥ ንግድ፣ አዋኪ ተግባራት፣ ሕገ ወጥ ማስታወቂያና በሌሎች የደንብ ጥሰቶች ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ የኮንፈረንስና የቱሪስት ማዕከል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ለእንግዶች ደረጃውን የጠበቀ እርድ ማከናወን እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ በበኩላቸው÷ ጤንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ የእርድ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በከተማ አስተዳዳሩ በየመንደሩ የሚደረግ ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድ ሒደት እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።

የእንስሳት እርድ በሕክምና ባለሙያዎች ተመርምሮ ጤንነቱ ከተረገጋጠ በኋላ ሕጋዊ እርድ በሚከናወንባቸው ቦታዎች ላይ መፈጸም አለበት ነው ያሉት።

ሕገ ወጥ እርድን ለመከላከልም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረትና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ የከተማ ግብርና ኮሚሽን፣ የሆቴል ባለቤቶች እንዲሁም የልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!