የሀገር ውስጥ ዜና

በሀገራዊ ምክክር ሂደት አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ አድርገዋል – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) 

By Mikias Ayele

November 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)  በሀገራዊ ምክክር ሂደት አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ አድርገዋል አሉ።

ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶች እና የፖለቲካ ሀሳቦች ላይ ጥልቅ እና ግልፅ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መስፍን አረዓያ (ፕ/ር) በመድረኩ እንዳሉት÷ ኮሚሽኑ እያከናወነ በሚገኘው የምክክር ሂደት ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነዉ፡፡

ለምክክር ሂደቱ ውጤታማነት የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው÷ በምክክሩ ሂደቱ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

እስካሁንም በምክክር ሂደቱ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ በማንሳት÷ እነዚህ ፓርቲዎች በሚቀጥሉት ጊዜያት በምክክር ሂደቱ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ ለተነሳው ዓላማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የሁሉም አካላት ተሳትፎ ሲንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በአመለወርቅ መኳንንት