አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካ በብራዚል ቤሌም በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የ2025 የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ30) ላይ በአንድ ድምፅ በመናገር በዓለም ተደምጣለች አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አፍሪካ የመፍትሄ አህጉር ሆና ለቀጣይ ዘላቂነት ባለው ዓለም አቀፍ ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ አጋር ሆና ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን ኮፕ32ን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ በመመረጧ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ሀላፊነት ለኢትዮጵያ በመስጠቱ ያላቸውን ክብር ገልፀው፤ ይህ ዕውቅና በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ርምጃ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እምነት እንዳለው ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ አቅም እንዳላትም ያረጋገጠ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ ርምጃዎችን የሚያራምድ ኮፕ32ን ያካተተ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡