የሀገር ውስጥ ዜና

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሐይቅ ከተማ የተገነባውን ትምህርት ቤት መረቁ

By Mikias Ayele

November 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን የተገነባውን ትምህርት ቤት መርቀዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን በመጎብኘት እና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ስራ በማስጀመር ላይ ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለትም በበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን የተገነባውን የገበታ ለትውልድ ሐይቅ 1ኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መርቀዋል።

ትምህርት ቤቱ ከ1976 ዓ/ም ጀምሮ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም በእድሜ ብዛት እየፈራረሰ ይገኝ እንደነበር የትምህርት ቤቱ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ተናግረዋል።

አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ በባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ ድጋፍ እንደ አዲስ ተገንብቶ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ተፈጥሮለታል።

ለትምህርት ቤቱ ግንባታ 75 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ 16 የመማሪያ ክፍሎች አሉት።

ለትምህርት ቤቱ ከአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የመጽሐፍት ድጋፍ ተደርጓል።

በለይኩን ዓለም