አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 13፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ከ227 ቶን በላይ የተበላሹና አስገዳጅ የገላጭ ጽሁፍ መስፈርትን ያላሟሉ የምግብ ምርቶችና ጥሬቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደረገ፡፡
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በሀምሌ ወር ብቻ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አምስቱ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ባደረገው ቁጥጥር ነው የምግብ ምርቶቹን እና ጥሬ እቃዎቹን እንዳይገቡ ማድረግ የተቻለው፡፡
እነዚህም በጉዞ ወቅት የተበላሹ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እንዲሁም አስገዳጅ የገላጭ ጽሁፍ ያላሟሉ ከ227 ነጥብ 64 ቶን በላይ ምግብና የምግብ ጥሬ ዕቃ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተደረጉት ምርቶች ህብረተሰቡ በዕለት ተዕለት ኑሮ በስፋት የሚጠቀምባቸው ናቸውም ብሏል፡፡
የተበላሸ የምግብ ዘይትና ወተት፣ የተበላሸ የቲማቲም ድልህ፣ አስገዳጅ የገላጭ ጽሁፍ መስፈርትን ያላሟላ የምግብ ጥሬ ዕቃ እንደሚገኝበት ከኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡