የሀገር ውስጥ ዜና

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት ይፈታል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Adimasu Aragawu

November 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት ይፈታል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደሴ ከተማን መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ስራ አስጀምረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ደሴ ከተማ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ዘመን ተሻጋሪ ገድል የጻፈች፣ የሰለጠነ ማህበረሰብ የገነባች፣ የዘመናዊ መገለጫ ከተማ ናት፡፡

ህዝቡ አስተዋይ፣ ለፍትህ የቆመ፣ በውይይት የሚያምን፣ የሰላም አምባሳደር የልማት አርበኛ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወሎ ምድር ለኢትዮጵያዊነት የመደመር ቅኝት ማሳያ፣ ድንቅ እሴት እንደ ቦርከና ወንዝ ሞልቶ የሚፈስበት የአብሮነት እና የመዋደድ ተምሳሌት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ወሎ የጥበብ መፍለቂያና የዕውቀት ማዕድ መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የወሎዋ ዕምብርት ደሴ ከተማ አሁን በከፍተኛ የልማተ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በከተማዋ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማሳለጥ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች በማንዋል ሲሰጥ የቆየውን የመንግሥት አገልግሎት በአንድ ማዕከል ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዮችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ በህዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል፡፡

ብልሹ አሰራርን በማስወገድ ዘመኑን የዋጀና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸው÷ በደሴ ከተማ የተሰራው ማዕከል የህዝቡን የረጅም ጊዜ የፈጣን አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በለውጡ መንግሥት ደሴ የብልፅግና ብርሃን ወጋገን ፈንጥቃለች፣ ለኗሪዎቿ ምቹ የበለፀገች እና የተዋበች ከተማ መሆን የሚያስችላትን የተስፋ ጎዳና ጀምራለች ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የደሴ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት እየገለጠ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለተሻለ አፈጻጸም ህዝቡና አመራሩ ተጋግዞ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሰላምና ልማት ተመጋጋቢ መሆናቸውን ገልጸው÷ የተጀመረው ልማት ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!