አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በተለያዩ ሥነ ምህዳሮች የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን የማፍለቅ አቅማችን አድጓል አሉ።
ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የዝርያ ማሻሻል ምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ኢንስቲትዩቱ፤ በጥናትና ምርምር፣ ቴክኖሎጂዎችን በማሰራጨት እንዲሁም አገልግሎትና ድጋፍ በመስጠት አሰራር እና ማሻሻያዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ለሁሉም ሥነ ምህዳር እና ወቅቶች ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ምርምር ያለማቋረጥ ይከናወናል።
ለዚህም ለደጋ፣ ወይና ደጋ እና ቆላማ አካባቢዎች ተስማሚና ውጤታማ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ የሚያስችሉ የግብርና ምርምር ማዕከላት በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ተቋቁመው እየሰሩ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ወደ ማምረት የተሸጋገረው አርሶ አደሩ ለበጋም ሆነ ለክረምት ወቅት የሚስማማውን የተሻሻለ ዝርያ ሊያገኝ ይገባል ነው ያሉት።
ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ኢንስቲትዩቱ እንደወቅቱ ሁኔታ ምርት መስጠት የሚያስችሉ ዝርያዎችን በማፍለቅ ተደራሽ እያደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
ለአብነትም የቆላ፣ የወይና ደጋ፣ የደጋ፣ የእርጥበታማ፣ የዝናብ እና የመስኖ በሚሉ መስፈርቶች ተለይተው በምርምር የፈለቁ የተሻሻሉ የበቆሎ፣ ማሽላ እና ስንዴ ዝርያዎች እንዳሉ አንስተዋል።
የኢንስቲትዩቱ የሰብል ማሻሻያ መርሐ ግብሮች ለተለያዩ ሥነ ምህዳሮች እና ወቅቶች ተስማሚ ዝርያዎችን የመለየትና የማፍለቅ አቅም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)፤ ይህንን አቅም አጠናክሮ በማስቀጠል የግብርና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በአቢይ ጌታሁን
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!