አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጠበቁ እና እንዲለሙ በማድረግ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት እንደ ሀገር ዕመርታ የታየበት ነው አለ።
አገልግሎቱ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎች እንዲታወቁ፣ እንዲለዩ እና እንዲገለጡ የተሰጠው ትኩረት ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ተደማሪ አቅም መፍጠር መቻሉን ገልጿል።
ይህ ተግባርም ክልሎችበአካባቢያቸው የሚገኙ ፀጋዎችን አልምተው ዜጎች ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጡበት መልካም ዕድል እንደሆነ አመላክቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ዓለም አቀፍ የጢያ ትክል ድንጋይ ቅርሶች እና ምድረ ከብድ አቡነ ገብረ-መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም የሚጠቀሱ መሆናቸውን አገልግሎቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አውስቷል።
ጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ሆኖ በ1972 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ ና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ቢመዘገብም ትኩረት ተነፍጎት የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች ሳይሟሉለት መቆየቱን አንስቷል።
ነገር ግን አሁን ላይ የኢትዮጵያ ጸጋዎችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተጀመረው ጉዞ መካነ ቅርሱ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እየተሟሉለት ይገኛል።
በዚህም ሁለት ከተሞችን የሚያገናኝ፣ ባለሀብቶችን በማስተባበር የሚሰራ እና ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚፈልግ “ጢያ ፕሮጀክት” በሚል የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ፕሮጀክቱ በርካታ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጥር የቻለ እና የአከባቢው ፀጋ የሚገለጥበት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመረጃው ጠቁሟል።