የሀገር ውስጥ ዜና

ኢንስቲትዩቱ ከሀገራዊ ሕልምና ራዕይ ጋር የተሰናሰሉ ጉዳዮች የታዩበት ነው – ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

November 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሀገራዊ ሕልም እና ራዕይ ጋር የተሰናሰሉ ጉዳዮች የታዩበት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ጽ/ቤትን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት÷ ኢንስቲትዩቱ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሃሳባችው እንዲወለድ የሚያደርግ የመልካም እሳቤ ውጤት ነው።

በተቋሙ ወጣቶች ሃሳባቸውን ይዘው በመምጣት እና በመታገዝ ራዕያቸው እውን እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ከኢንዱስትሪው ጋር በመገናኘት ወደ ቢዝነስ እንዲያድጉ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ አስደናቂ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ከ200 በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመው ÷ ይህም መንግሥት ትውልድ ላይ መስራት እንዳለበት የሚያመላክት እና የሚጨበጥ ተግባር የታየበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በመንግሥትና ሃሳብ ባላቸው ወጣቶች መካከል ያለው ግንኙነት በት/ቤት ውስጥ በማለፍ ብቻ መወሰን እንደሌለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች እየታገዙ ሃሳቦቻቸውን እንዲያዳብሩ ማድረግ ከተቻለ በርካታ ሃሳቦች፣ ሥራዎች እንዲሁም ኩባንያዎች ይፈጠራሉ ብለዋል፡፡

አፍሪካ ውስጥ ጀምሮ መጨረስ አይቻልም፤ አትችሉምና አትሞክሩት የሚል መታረም ያለበት እሳቤ አለ ፤ ለወጣቱ አስቻይ ሁኔታ ፣ፖሊሲ እና የሚሞክርበትን አውድ ከፈጠርንለት ጥሩ ውጤቶችን ማግኘት እንችላለን ነው ያሉት፡፡

አክለውም ከሀገራዊ ህልም እና ራዕይ ጋር ተሰናስለው የሚታዩ ጉዳዮች በተቋሙ መንጸባረቃቸው ለትውልድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ ያለበት ደረጃ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው÷ይህም ለኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ፋይዳ ያለው እና ትውልድ ነገ የሚኮራበት ስራ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

በርትቶ በመስራት የተሟላ ውጤት ማምጣትና ራዕይን ማሳካት እንደሚቻል አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ የጠራ እሳቤ መያዝ እና በቁርጠኝነት መስራት ኢትዮጵያውያን በርካታ ነገሮችን የሚማሩባቸው መሰል ተቋማትን ለማበራከት ያስችላል ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!