አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሁሪያ አሊ፡፡
የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሹ ጉዳዮች በሀገር ውስጥ እምቅ አቅምና እውቀት መፈታትን የሚያበረታታው ሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት በይፋ ተመስርቶ ሥራ ጀምሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ ወ/ሮ ሁሪያ አሊን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴዔታዋ በዚህ ወቅት÷ ከዚህ በፊት ለሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች የተጋለጡ አረጋውያንን በመደገፍ የሚታወቀው ሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ዛሬ ሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በሀገር ውስጥ አቅም ለመሸፈን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰው ተኮር በሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚያጠናክር ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
አረጋውያን በተለያዩ ዘርፎች የሚያስፈልጓቸውን ድጋፎች ለማጠናከርም ሄልፕኤጅ ኢትዮጵያን ከመሰሉ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ የቦርድ ኃላፊ ቶማስ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች የሚመሩባቸውን እሳቤዎች በሀገራዊ አውቀትና አካሄድ መምራትና ማስተዳደር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጉልህ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል፡፡
ይህም ዓለም አቀፋ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስራቸው በሙሉ በሀገር ውስጥ ዜጎች እንዲተዳደር እንዲሁም የየኔነት መንፈስ አንዲሰፍን የጎላ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
ሄልፕኤጅ በዘርፉ ለተሰማሩ ለሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደ አርአያ ሊወሰድ የሚችል ልምድ አለው ያሉት ደግሞ የሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በላቸው ናቸው፡፡
ሄልፕኤጅ ባለፉት 33 ዓመታት ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሆኑ አረጋውያን በማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች እና የኑሮ ድጋፍን ጨምሮ ዘላቂ እና በቂ ገቢ እንዲያገኙ ማደረጉን ተናግረዋል
ሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ በዚህ ለውጥ ውስጥ በሀገራዊ እሳቤና ተነሳሽነት የጀመራቸውን ሥራዎች ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
ድርጅቱ በማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች እና የኑሮ ድጋፍን ጨምሮ አረጋውያን ዘላቂ እና በቂ ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውንም ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡