ስፓርት

11 ግቦችን ያስቆጠረው ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል…

By Abiy Getahun

November 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም እግር ኳስ ከተመለከታቸው ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ ነው የማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞ ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል፡፡

ፒተር ሽማይክል ከኮከብ ግብ ጠባቂነቱ በተጨማሪ ጨዋታ የማንበብ ብቃቱ እና ለቡድን አጋሮቹ ኳስ በእግሩ የሚያቀብልበት መንገድ ልዩ ነው፡፡

ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን የማስጀመር እና ለቡድን አጋሮቹ ረዘም ያሉ ኳሶችን የማቀበል ልዩ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ መሆኑም ይታወሳል፡፡

ዴንማርካዊው የቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ለሀገሩ እና ለተጫወተባቸው ክለቦች በአጠቃላይ 11 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

በተደጋጋሚ ግቦችን ማስቆጠር በግብ ጠባቂዎች ዘንድ የተለመደ ባይሆንም ፒተር ሽማይክል ግን በተደጋጋሚ ማሳካት ችሏል፤በተከላካዮች የሚስተዋሉ ስህተቶችን ጮክ ብሎ በመናገር የሚታወቅ ድንቅ ግብ ጠባቂም ነበር፡፡

ተጫዋቹ በማንቼስተር ዩናይትድ ቆይታው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ በፈረንጆቹ 1998/99 የውድድር ዓመት የሶስትዮሽ ባለክብር ሲሆን ÷ የዴንማርካዊው ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል ሚና የሚተካ አልነበረም፡፡

ፒተር ሽማይክል የእንግሊዝ ፕሪሚየር እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የውድድር ዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማትን ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡

በፈረንጆቹ 1992 ከሀገሩ ዴንማርክ ጋር የአውሮፓ ዋንጫ ማሳካት የቻለው ፒተር ሽማይክል ÷ በወቅቱ የዓለም ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ ተመርጧል፡፡

በፈረንጆቹ 2001 ሬውተርስ ባሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት በወቅቱ የነበሩትን ግብ ጠባቂዎች በመብለጥ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡

ለማንቼስተር ዩናይትድ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ አስቶንቪላ እና ማንቼስተር ሲቲ ተጫውቶ ያሳለፈው ሽማይክል በአጠቃላይ በክለብ ሕይወቱ 748 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡

ለሀገሩ ዴንማክ ከፈረንጆቹ 1987 ጀምሮ ግልጋሎት የሰጠው ግብ ጠባቂው የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች 129 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡

በማቼስተር ዩናይትድ በቆየባቸው ዓመታት ስኬታማ ጊዜን ማሳለፍ የቻለ ሲሆን÷ በአጠቃላይ በእግር ኳስ ሕይወቱ 24 ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

ለማንቼስተር ዩናይትድ ስምንት የውድድር ዓመት መጫወት የቻለው ፒተር ሽማይክል÷ ለከተማ ተቀናቃኙ ማንቼስተር ሲቲ ደግሞ ለአንድ የውድድር ዓመት ያህል ተጫውቷል፡፡

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በነበረው ትልቅ ስኬት የሊጉ የምንጊዜም ምርጦች እና ዝነኞች መዝገብ ላይ መስፈሩ ይታወሳል፡፡

ከምን ጊዜም ምርጥ ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው የማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞ ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል በፈረንጆቹ 1963 በዛሬዋ ዕለት ነበር የተወለደው፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ