አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እያከናወነ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተመናምነው የነበሩ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች እንዲጎለብቱ ማድረግ ተችሏል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
አገልግሎቱ ባወጣው መረጃ መንግስት ለተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ በሰጠው ልዩ ትኩረት መላ ሕዝቡን ያሳተፈ ውጤታማ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የደን ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብሏል።
በተለይም ሕብረተሰቡ በነባር ዕሴቶች ጠብቆ ያቆያቸውና በጊዜ ሂደት እየተመናመኑ የመጡ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መልሰው እንዲጠነክሩ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ገልጿል።
በዚህም ብዝኃ ሕይወቱ መልሶ እንዲያገግምና አካባቢዎቹ የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ መልካም ዕድል ተፈጥሯል ነው ያለው።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን ሕብረተሰቡ ፀጋውን አውቆ የተፈጥሮ ሀብቱን ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ የሚያስተላልፈው ቅርስ መሆኑንም ገልጿል።
ከ350 ሄክታር በላይ የሚሸፍነው ከ700 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን በአካባቢው ልማድ መሠረት በማሕበረሰቡ ቃልኪዳን (በጉርዳ ሥርዓት) ተጠብቆ የኖረ መሆኑንም አመላክቷል፡፡
ጥብቅ ደኑ በርካታ የዕጽዋት ዝርያዎች ያሉበት ሲሆን÷ እንደ ወይራ፣ ዝግባ፣ የሀበሻ ፅድ፣ የኮሶ ዛፍ የመሳሰሉትን ጨምሮ የተለያዩ አይነት የዱር እንስሳት እና የወፍ ዝርያዎችን ይዟልም ነው ያለው በመረጃው፡፡
የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን የዝናብ ሥርጭትን በማስተካከል የአካባቢውን ምርታማነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን÷ በሥራ ዕድል ፈጠራና ቱሪዝም ዘርፉም በርካታ አስተዋጽዖ የሚያበረክት መሆኑን አስረድቷል፡፡
በምንጭ የተከበበው የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን በውስጡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ መስጂድ፣ ገዳም እንዲሁም የጤና አገልግሎት መስጫዎችን አካትቶ ይዟል።
በአካባቢው ለተከታታይ ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ነባር የተፈጥሮ ጥብቅ ደኑ የበለጠ እንዲጠናከር አድርጓል ሲልም አገልግሎቱ ጠቅሷል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!