አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት መኖ አቅርቦትና አጠቃቀም በማሻሻል የእንስሳት መኖ ዋስትና ለማረጋገጥ ውጤታማ ስራዎች እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ እንስሳት በማምረት አቅማቸው ልክ ምርት መስጠት እንዲችሉ፣ ፈጣን ዕድገት እንዲኖርና በሽታን የመቋቋም አቅም ለመፍጠር የመኖ ዋስትናን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡
በተመሳሳይ ጥራት ያለውን ምርት በማምረት የእንስሳት ሀብቱ እያበረከተ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ አስተዋፅዖ ለማሳደግ የመኖ አቅርቦት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻለ መኖ ማልማትና ምጥን መኖን በማቀነባባር አቅርቦቱን በመጠን፣ በጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የመኖ አቅርቦትና ጥራትን ለማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ እንደየአቅሙ ባለው የመሬት መጠን የሚተገበር 1 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት በነፍስ ወከፍ የማልማት ክልላዊ የተሻሻለ መኖ ልማት ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
ይህም የእንስሳት መኖ አቅርቦት ይዘትን ለማሳደግና ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ለዜጎች የስራ እድል እና አማራጭ የገቢ ምንጭ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በክልሉ የወተት፣ የስጋ፣ የእንቁላል ምርታማነት ለማሻሻል የምጥን መኖ አቅርቦትን ለማሳደግ የመኖ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዘርፉን ለማጠናከር በተሰራው ስራ በ2017 በጀት ዓመት ከ42 ሺህ ቶን በላይ የተቀነባበረ መኖ ማቅረብ ተችሏል ያሉት አቶ ኡስማን÷ በክልሉ በሕብረት ስራ ማሕበራት፣ በተደረጁ ወጣቶችና በግል ባለሃብቶች የሚተዳደሩ ከ14 በላይ የመኖ ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ወጣቶች ተደራጅተው ተጨማሪ የመኖ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጥሩ ለማስቻል እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።
በ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መኖ መልማቱን ጠቅሰው÷ 11 ሺህ ቶን የተቀነባበረ መኖ ለገበያ ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል።
እስካሁን በተሰራው ስራ የመኖ አቅርቦት በይዘትና በመጠን ተደራሽ በመሆኑ የሌማት ትሩፋት ግቦችን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።
በዚህም የምግብና ሥነ ምግብ ዋስትናን በቤተሰብ፣ በማሕበረሰብ እና በክልል ደረጃ በማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ለግብርና ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት ለማቅረብ እና ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ምንጭ እንዲሆን የሚደረገው ርብርብ ውጤታማ እንዲሆን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በአድማሱ አራጋው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!