የሀገር ውስጥ ዜና

ከተማና ከተሜነት የዓለም ለውጥ መነሻና የእድገት መዳረሻ ነው – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

By Mikias Ayele

November 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተማና ከተሜነት የዓለም ለውጥ መነሻ እና የእድገት መዳረሻ ነው አሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፡፡

በሰመራ-ሎጊያ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የከተሞች ፎረም የመዝጊያ ሥነ-ስርዓት ላይ ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የሰው ልጆች ሁሌም በማደግና መለወጥ ፍላጎት ውስጥ እንደመገኘታቸው ከተሞችን ይፈጥራሉ፣ ወደ ከተሞች ይተምማሉ፣ ከተሞችንም ያሳድጋሉ ብለዋል፡፡

ተዓምራዊ በሚመስል መልኩ በለውጥ ፍጥነት እየገሰገሰች በምትገኘው ዓለም ውስጥ ከተማና ከተሜነት የዚህ ለውጥ መነሻ፣ የከፍታውም መድረሻ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓለም ለውጥ እና ዘመናዊነት አካል የሆነችው ኢትዮጵያ ከለውጡ ጋር እኩል ለመጓዝ በመንግሥት ደረጃ ከተሞችን በተመለከተ ፖሊሲ እና ግብ በማስቀመጥ በተከናወነው ስራ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ ከህብረተሰቡ ህይወት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በቂ ትኩረትና ክትትል ካላገኘ ቅሬታ የሚያስከትል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በተለይም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለረዥም ጊዜ ከፍተኛ የህዝብ እሮሮ ያለበትና ስር ነቀል በሆነ መንገድ መቅረፍ ያልተቻለ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ህብረተሰቡን ያረኩና አብነት የሚሆኑ የማዘጋጃ ቤቶች አገልግሎቶችን በመለየት ለሌሎች በተሞክሮ መልክ ሊሻገሩ የሚችሉበትን ስልት መቀየስ ይገባል ብለዋል።

የማዘጋጃ ቤታዊ  ገቢዎች መጨመራቸው እንደ ትልቅ ስኬት የሚነሳ  መሆኑን በመጥቀስ ከተሞች በሰበሰቧቸው ገቢዎች በሚታይ ደረጃ ልማቶቻቸውን እንዲያፋጥኑ አሳስበዋል፡፡

በከተሞች ሴፍቲኔትና ምግብ ዋስትና ስራዎች ከድህነት ወለል በታች ያሉ የከተማ ነዋሪዎችን የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የከተማ ነዋሪዎች በዘላቂነት የተሻለ የኑሮ ለውጥ እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በከተማ የመኖሪያ ቤት ልማት የተሻለ አቅጣጫ በመከተል በማህበራት፣ በመንግስትና በባለሃብቶች ጥምረት እንዲሁም በሌሎች አማራጮች በመስራት ውጤቶችን ማየት ችለናል ብለዋል፡፡

ከተሞች የአረንጓዴ ልማት ስፍራዎች በማዘጋጀት እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

የከተማ መሬት አጠቃቀም በዘመናዊ የመረጃ ስርአት ተደግፎ እንዲተዳደር በማድረግ የመሬት ሀብት ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችሉ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ችግሮችን ለመፍታትና ዘርፉን በተሻለ ለመምራት የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በቀጣይ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታን፣ የቤቶች ልማት፣ የገቢና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያን፣ የአረንጓዴ መሰረተ ልማትን የመሬት ማኔጅመንትና የከተማ ፕላን  ትግበራ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።