የሀገር ውስጥ ዜና

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ የባሕል ለውጥ አምጥቷል – አቶ ጥላሁን ከበደ

By Abiy Getahun

November 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ የክረምት የበጎ ፈቃድ ማጠቃለያ እና የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ እንዳሉት፤ የ2017/18 ክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ15 ልዩ ልዩ ተግባራት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ተሰጥቷል።

በዚህም ወጣቶች ያሳኩት ስራ በክልሉ ማህበራዊ መስተጋብር ላይ የሕዝብ ለህዝብ ትስስርን መፍጠር ችሏል በማለት ገልጸው፤ የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሰዉ ተኮር የሆነው ብልጽግና ፓርቲ አቅም የሌላቸው ወገኖች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚሰራው ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አመራሩ ላስመዘገበው ውጤት እውቅና የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማጠናከር የወንድማማችነት ትርክት ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ በክረምቱ ከ2 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ከተሰሩት ስራዎች ውስጥ ከ9 ሺህ 200 በላይ ቤቶች ግንባታ እና ከ6 ሺህ 400 በላይ ቤቶች እድሳት እንደሚገኝበት ጠቅሰው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክልሉ መሻገር እንደሚችል የታየበት ቁልፍ ተግባር ነው ብለዋል።

የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት ይህንን መልካም ዕሴት በማጠናከር ጠንካራ የስራ ባህል እንዲዳብር በዘርፉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ካሰች ኤልያስ ናቸው።

በመለሰ ታደለ