አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ1920ዎቹ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ 12 ውድ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ተረክቧል፡፡
ታዋቂው የኒውክሌር ሳይንስ ፕሮፌሰር ራሞን ቫይስ አያታቸው ከ100 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የጀርመን ልዑክ በነበሩበት ጊዜ በስጦታና በግዥ አሰባስበው ያቆዩአቸውን ቅርሶች ነው በዛሬው ዕለት ለተቋሙ ያስረከቡት፡፡
በመርሐ ግብሩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ ፈርዲናንድ ቮን ቬይሄ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ሰላማዊት ካሳ በዚህ ወቅት ÷ የራሞን (ፕ/ር) ቤተሰቦች ቅርሶቹን ጠብቀው በማቆየትና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ለኢትዮጰያ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ስለገለጡ አመስግነዋል፡፡
ዛሬ ከተበረከቱት ውድ ቅርሶች ውስጥ ዘውዶች፣ ጋሻዎች፣ ጎራዴ፣ ዝናር፣ ስእሎች እንዲሁም ከራስ ተፈሪ መኮንን የተበረከቱ ስጦታዎች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተጨማሪ ሃብቶች ከመሆናቸው ባለፈ ለጥናት እና ምርምር በግብዓትነት እንደሚያገለግሉ አውስተዋል፡፡
በመላው ዓለም በግለሰቦች እጅ እና በተቋማት ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪክ አስረጂ የሆኑ ጥንታዊ ቅርሶችን ወደ ሀገር የመመለሱ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደቤታቸው መመለስም ከሀገራቱ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር አስገንዝበዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ