አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ዋንጫ፣ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግና ባሎንዶር በታሪክ ካሸነፉ 10 ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው ሪካርዶ አዜክሰን ዶስ ሳንቶስ ሌይቴ (ካካ)፡፡
ትውልዱ በፈረንጆቹ 1982 በብራዚል ጋማ የሆነው አመለ ሸጋው ተጫዋች እግር ኳስን በሀገሩ ክለብ ሳኦ ፖሎ አካዳሚ ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ በመጫወት አድጓል፡፡
በቀጣይም በ2001 በ18 ዓመቱ ለሳኦ ፖሎ ዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል፡፡
በፈጣን ሩጫው፣ ብዙ ተጫዋቾችን በማለፍ እንዲሁም ኳስ በማቀበል ልዩ ተሰጥኦውና ግብ በማስቆጠር ድንቅ ብቃቱ የሚታወቀው ካካ ከሁሉም በላይ በመልካም ሥነ ምግባሩ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅ ነው፡፡
በ2003 ወደ ጣልያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን የተዛወረ ሲሆን ÷ በዚህም እጅግ ስኬታማ ስድስት ዓመታትን በሚላን ከተማው ክለብ አሳልፏል፡፡
በክለቡ በቆየባቸው ዓመታት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የነበረው ካካ ÷ በ2006/2007 የውድድር ዓመት የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ሲያሸንፍ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በውድድር ዓመቱ ባሳየው አስደናቂ አቋምና ብቃትም የዓመቱ የፊፋ ኮከብ ተጫዋች ከመሆን ባለፈ የባሎንዶር ሽልማትን ተቀዳጅቷል፡፡
ከሚላን ስድስት ስኬታማ ዓመታት ቆይታ በኋላ በ2009 ለሪያል ማድሪድ በወቅቱ ሁለተኛው ውድ የዝውውር ዋጋ በሆነ 67 ሚሊየን ዩሮ ተዘዋውሯል፡፡
በሪያል ማድሪድ የተጠበቀውን ያህል በተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት ስኬታማ ጊዜያትን ያላሳለፈው ካካ ለክለቡ ባደረጋቸው 120 ጨዋታዎች 29 ግቦችን በአራት ዓመታት ቆይታው አስቆጥሯል፡፡
በ2013 ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ ኤሲ ሚላን በውሰት የተመለሰው አመለ ሸጋው ተጫዋች ለአሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከር ክለብ ኦርላንዶ ሲቲ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡
ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን በ2002 የመጀመሪያ ጥሪ የደረሰው ካካ በወቅቱ የዓለም ዋንጫን ለሀገሩ ከፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን ÷ ለብራዚል 92 ጊዜ ተጫውቶ 29 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡
በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ስፖርተኞች መካከል አንዱ ሲሆን ÷ በወቅቱ 10 ሚሊየን የትዊተር ተከታዮችን በማፍራት ቀዳሚ ነበር፡፡
ሪካርዶ ካካ ከእግር ኳስ በተጨማሪ በሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን ÷ በ2004 የዓለም ምግብ ፕሮግራም በእድሜ ትንሹ አምባሳደር መሆን ችሏል፡፡
በእግር ኳስና ከእግር ኳስ ውጪ ባሉ ሥራዎቹ ባበረከተው በጎ አስተዋጽኦም በ2008 እና 2009 በታይም መጽሔት የዓለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ አይዘነጋም፡፡
አመለ ሸጋው ሪካርዶ አዜክሰን ዶስ ሳንቶስ ሌይቴ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታሕሳስ 2017 በ35 ዓመቱ ጫማውን መሥቀሉ ይታወሳል።
በአቤል ነዋይ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!