አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዛሬም ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት በትራፊክ አደጋ እያጣን ነው አለ።
በሚኒስቴሩ የመንገድ ደህንነት አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ለማ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በቁጥር ደረጃ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም የማይተካው የሰው ሕይወት እየጠፋ በመሆኑ አደጋው ቀነሰ የሚለው ገላጭ ቃል አይደለም ብለዋል፡፡
የህዝብና ተሽከርካሪው ቁጥር ልዩነቱ የሰፋ ቢሆንም በአፍሪካ እየደረሰ ያለው የመኪና አደጋ የዓለምን 90 በመቶ የሚሸፈን ሲሆን በጥቂት ተሽከርካሪ ብዙ አደጋ የሚደርስበት አህጉር ሆኖ መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግበው ያሉ ተሽከርካሪዎች 1 ሚሊየን የማይሞሉ እንደነበር አንስተው፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት 5 ሺህ 118 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውሰዋል።
በ2017 ዓ.ም ሪፖርት መሠረት በሀገሪቱ በአጠቃላይ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ተሽከርካሪዎች እንደነበሩና በዓመቱ 3 ሺህ 799 ሰዎች በመኪና አደጋ መሞታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም በአንጻራዊነት ቅናሽ የታየበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ የመኪና አደጋን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ለዚህም አመቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ማበልጸግ ሥራዎችን ከኢትዮ ቴሌኮምና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር እየተሠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አሽከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተቋማት፣ እግረኛውና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሁሉም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በሄኖክ በቀለ
አቶ ዮሐንስ ለማ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሙሉውን ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ https://youtu.be/fZykkEZT7gE?si=pNq2xp6ZUybvMDVI