አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ሁለት እውቅናዎችን ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማሕበር አገኘች።
ኢትዮጵያ እውቅናውን ያገኘችው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ለነበረው ሚና እንደሆነ ተገልጿል።
የእውቅና ሥነ ሥርዓቱ በብሔራዊ ሙዚዬም የተከናወነ ሲሆን÷ ስፖርት ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ ጉልህ ማሳያ መሆኑ ተነስቷል።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሩጫ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክና ቦታ አለው ብለዋል።
ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣሊያን ሮም በተካሄደው የኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ታሪካዊ ድል በማስመዝገብ ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣቱን አስታውሰዋል።
በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጀግና አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት የመዲናችን ብሎም የኢትዮጵያ መገለጫና ተናፋቂ የአደባባይ ስፖርታዊ ክንውን ነው ብለዋል።
በሁለቱ ዘርፎች ዕውቅና መሰጠቱ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላን፣ የታላቁ ሩጫ ውድድር መስራች አትሌታችን ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን እና ውድድሩን ባማረ ሁኔታ ሲያካሂዱ የቆዩትን ሁሉ አመስግነዋል።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ዳይሬክተር ክሪስ ተርነር ተገኝተዋል።
በጀማል አህመድ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!