የሀገር ውስጥ ዜና

በቅንጅት መስራት የሚጠይቀው የግብርና ኢንሹራንስ…

By Adimasu Aragawu

November 20, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አርሶ አደሮች የግብርና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንዲሆንና የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የዘርፉን ተደራሽነት ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።

በብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር በላይ ቱሉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የግብርና ኢንሹራንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለአርሶ አደሮች የሚያቀርቡበትን አስቻይ ሁኔታዎች የሚፈጥሩ የሕግ ማዕቀፎች የማዘጋጀት ስራዎች ተከናውነዋል።

ብሔራዊ ባንክ ለኢንሹራንስ ተቋማት አስቻይ የሕግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ባለፈ አዲስ መመሪያ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝና የተለያዩ የማማከርና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ አንስተዋል።

ኩባንያዎች ተገቢውን አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው መሆኑንና ጉዳት ሲደርስ ለአርሶ አደሮች በፍጥነት የሚከፈልበትን ሁኔታዎች የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ይህም ተጠቃሚዎች በዘርፉ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለማስቻል እንደሆነ አስረድተው÷ አርሶ አደሮች ከሚያጋጥማቸው አደጋ እንዲያገግሙና መልሶ እንዲጠናከሩ ለማስቻል የግብርና ኢንሹራስ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መድሕን ሰጪዎች ማሕበር ፕሬዚዳንት ያሬድ ሞላ በበኩላቸው÷ በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከሚያጋጥሙ ችግሮች አርሶ አደሩን ማሕበረሰብ ለመታደግ የግብርና ኢንሹራንስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ያካተቱ በርካታ የግብርና መድሕኖች ቢኖሩም ተደራሽነቱ በጣም ውስን እንደሆነ ገልጸው÷ የግንዛቤ አለመኖርና ከአርሶ አደሮች ጋር ትስስር ለመፍጠር አስቸጋሪ መሆኑ ተደራሽነቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል።

መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ የፋይናንስ ተቋማትና የግብርናው ዘርፍ ተዋንያን በትብብር የሚሰሩበትን ብሔራዊ የግብርና መድሕን ፕሮግራም በመንደፍ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ ይህንንም ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!