አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀዋሳ ከተማ ግብርን በአግባቡ በመሰብሰብ ከተማዋንና ህዝቧን የሚመጥን ስራ ይሰራል አሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጥራቱ በየነ።
ከንቲባው በከተማዋ ከሚገኙ የንግዱ ማሕበረሰብ ጋር በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ከተማዋ ካላት እምቅ አቅም አንፃር ኢኮኖሚዋ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ አለመቻሉን ገልጸው÷ ለዚህም የንግዱ ማሕበረሰብ የህግ ተገዢነት አናሳ በመሆኑ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ከተማዋን እና ህዝቧን የሚመጥን የልማት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት እንደ ኮሪደር ልማት፣ መንገድ፣ ውሃ እና የመኖሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ በከተማዋ የተጀመሩ ሰፋፊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ከተማዋን ዘመናዊና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ለእቅዱ መሳካትም የንግዱ ማሕበረሰብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት 6 ቢሊየን 461 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ በመጀመሪያው ሩብ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
በነፃነት ሰለሞን