ስፓርት

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሰባት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

By Adimasu Aragawu

November 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ12ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

ቀን 9 ሰዓት 30 ላይ ቼልሲ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በርንሌይን በሚገጥምበት ጨዋታ 12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መደረግ ይጀምራሉ፡፡

በ20 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቼልሲ በሊጉ ተከታታይ 3ኛ ጨዋታውን ድል ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

ባለሜዳው በርንሌይ በበኩሉ በሊጉ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላ የሊጉ ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ኖቲንግሃም ፎረስትን ያስተናግዳል፡፡

በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመራው ሊቨርፑል ወደ ድል ለመመለስ ሲጫወት ተጋጣሚው ኖቲንግሃም ፎረስት በበኩሉ ተከታታይ 2ኛ ድሉን በሊጉ ለማሳካት ይፋለማል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት ወልቭስ ከክሪስታል ፓላስ፣ ፉልሃም ከሰንደርላንድ፣ ብራይተን ከብሬንትፎርድ እንዲሁም ቦርንማውዝ ከዌስትሃም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ምሽት 2 ሰዓት 30 ላይ ኒውካስል ዩናይትድ ከማንቼስተር ሲቲ በሴንት ጀምስ ፓርክ ይገናኛሉ፡፡

ማንቼስተር ሲቲ በሊጉ ተከታታይ 3ኛ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ ሲገባ ኒውካስል ዩናይትድ በበኩሉ ከተከታታይ ሁለት ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ