አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ውጤትና ስኬታማነት የተንጸባረቀባት ውብ እና ጽዱ ከተማ ሆናለች አሉ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ በዚህ ወቅት ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለእሳቸውና ልዑካን ቡድናቸው ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያቸውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ አዲስ አበባ በማድረጋቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን የጎበኙት በፈረንጆቹ 1964 እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ እያደረጉት የሚገኙት የሥራ ጉብኝትም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነትና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በአዲስ አበባ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንደጎበኙ ጠቁመው ÷ በዚህም አዲስ አበባ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማነት የተንጸባረቀባት ውብና ጽዱ ከተማ ሆናለች ሲሉ አውስተዋል፡፡
ሲንጋፖር እና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት እና ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህም ሀገራቱ በኢኮኖሚ እና ሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መሰረት እንደሚጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ