አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ዲጂታል ክህሎትን በመገንባት ተወዳዳሪነትን እየፈጠረች ነው አሉ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ።
የፖሊሲ እና የቁጥጥር ስምምነት ለአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ተወዳዳሪነት፥ የኢትዮጵያ ጉዞ ወደ አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻልና በመሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በርካታ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
ኢትዮዽያ ደንቦችን በማጣጣም የአነስተኛ የንግድ ተቋማትን ተሳትፎ በማሳደግ ተወዳዳሪነትን እየፈጠረች ነው ብለዋል።
የታቀዱ ሪፎርሞች ትግበራ፣ መሠረተ ልማቶችን ማሻሻልና ለሴት የሥራ ፈጣሪዎች የሚደረግ ድጋፍ የድንበር ተሻጋሪ ንግድን ቀላልና የበለጠ አሳታፊ ያደርጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በመጠቀም የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማጎልበት፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና ለወጣቶች እድሎችን ለመፍጠር እየሰራች ነው።
በወንድማገኝ ጸጋዬ