አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና ምርትን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ የተጀመረው ጥረት መጠናከር አለበት አሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ቡና አምራቾች፣ ላኪዎች እና የዘርፉ ባለድርሻዎች በተገኙበት ሀገር አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና እውቅና መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተዘጋጀው መርሐ ግብሩ ‘ፈጠራ እና ፍጥነት ለቡናችን ስኬት’ በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቡና አቅራቢ ብቻ ሳትሆን ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀች ሀገር ናት።
ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ለህዝቡ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ጠቅሰው፤ ባለፈው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገባቱን ተናግረዋል።
የቡና ምርትን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፤ የቡና ዘርፉን ጨምሮ እድገትን የሚያፋጥኑ የኢኮኖሚ ሪፎርምን ተግባራዊ በማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የቡና ምርት የንግድ እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ የንግድ ማዕቀፎች ላይ አባል እና ስምምነቶችን በመፈጸም ላይ በመሆኗ የዘርፉ ተዋንያን ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ ቡና የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም ኢትዮጵያ በሚገባ ሳትጠቀምበት ቆይታለች ነው ያሉት።
ከለውጡ ወዲህ በተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ በዚህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ከቡና ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቷን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም 3ኛ የቡና አምራች ሀገርነት ደረጃን መያዝ መቻሏን ጠቅሰው፤ ለዚህም መንግሥት የግብይት ሰንሰለቱ የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ ያከናወነው ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ስኬት በሻይ እና በቅመማ ቅመም ዘርፍም ለመድገም ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ አመላክተዋል።
በዮናስ ጌትነት