አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የታዳጊ ሀገራትን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ፍትሃዊና አካታች የዓለም ሥርዓት እንዲኖር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናት አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ በሚገኘው 7ኛው የአፍሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፍትሃዊና አካታች የዓለም ስርዓት እንዲኖር በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዓለም ውስብስብና ተያያዥነት ያለውን ፈተና እየተጋፈጠች ባለችበት በዚህ ወቅት እነዚህን ፈተናዎች ለመሻገር አካታችነትና በጋራ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የታዳጊ ሀገራትን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ፍትሃዊና አካታች የዓለም ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ እና ትርጉም ያለው ውክልና ሊኖራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ፍትሃዊ የባለብዙ ወገን የፋይናንስ ስርዓት እንዲሁም የሁሉንም ወገን እኩል ተሳትፎ የሚያንጸባርቅ የዓለም ስርዓት እንዲኖር በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡