አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኬንያ እና ኡጋንዳ በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ እና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የሚያደርጉት ትብብር ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ጥሩ ምሳሌ እየሆነ ነው፡፡
አፍሪካውያን ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በመሰረተ ልማት አስተሳስሮ በወንድማማችነት መንፈስ በሚገባ መጠቀም ላይ ውስንነት እንዳለባቸው በስፋት ይነሳል፡፡
ሀገራቱ በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ ጎረቤቶቻቸውን አስቀድመው በቅንጅትና በትብብር በመስራት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገታቸውን ማሳላጥ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ይገለጻል፡፡
ለአብነትም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በተፈጥሮ ሃብት የካበተ ከመሆኑ ባሻገር ከፍተኛ የጂኦ ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው፡፡
ይሁን እንጂ በአካባቢው ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ባለመኖሩ ሀገራቱ ለድህነት፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ ፍልሰት እና ለሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተጋላጭ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እንደ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና አፍሪካ ህብረት ያሉ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ተቋማት የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመቅረጽ ውጤት ለማምጣት እየጣሩ ይገኛል።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ትስስርን ለማምጣት በሀገራት መሪዎች ዘንድ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር ደግሞ ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
አሁን ላይም ችግሩን ለመፍታት እና የቀጣናውን የፖለቲካ ትርክት ለማረቅ የሀገራቱ መሪዎች እና ቀጣናዊ ተቋማት አዳዲስ የትብብር ማዕቀፎችን ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በፖሊሲ ደረጃ በፈረንጆቹ 2019 የተመሰረተው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የድንበር ትብብር እና በዓለም ባንክ የሚደገፈው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደት ለዘላቂ የኃይል አቅርቦት ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ስራ ከገቡም ሰነባብተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች በትብብር በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ አንጻር ከሰሞኑ ኬንያ እና ኡጋንዳ የፈጠሩት ትብብርም ለቀጣናው በአርአያነት የሚጠቀስ ተግበር ነው፡፡ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጎረቤታቸው ኡጋንዳ ባዘጋጀችው የኢንቨስትመንት ጉብኝት ላይ የክብር እንግዳ ነበሩ፡፡
ፐሬዚዳንቱ በመድረኩ ባደረጉት ንግግርም ኡጋንዳ ኬንያ ከሚገኘው ግዙፍ የነዳጅ አስተላላፊ ኩባንያ ኬፒሲ የአክሲዮን ድርሻ እንድትወሰድ ፈቃዴን ሰጥቻለሁ ሲሉ ለኡጋንዳ አቻቸው ዩዌሬ ሙሴቪኒ አረጋግጠዋል፡፡
የኬንያ መንግስት 65 በመቶ የሚሆነውን የኬፒሲ ድርሻ ለግሉ ዘርፍ ለመሸጥ መወሰኑን የገለፁት ዊሊያም ሩቶ ÷ ከኡጋንዳ በተጨማሪ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም የአክሲዮን ድርሻ መግዛት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በ1973 የተመሰረተው እና በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ የነዳጅ አስተላላፊ የሆነው ኬፒሲ ኩባንያ ለቀጣናው ሀገራት ነዳጅ በማቅረብ ረገድ ሃላፊነቱን ሲወጣ እንደነበር ጠቅሰው ÷ ኩባንያው የኬንያ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሀገራት ጭምር ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከኬፒሲ በተጨማሪም ሩቶ ከኬንያዋ ኤልዶሬት ከተማ ተነስቶ በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የሚደርስ እንዲሁም ዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ድንበር መድረስ የሚችል የጋራ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ሥራዎች መጀመራቸውን አመላክተዋል፡፡
አክለውም ሩቶ ኬንያ እና ኡጋንዳን በባቡር መስመር ለማስተሳሰር በቅርቡ ከኬንያዋ ኔቫሻ ከተማ ወደ ካምፓላ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚያደርስ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
ይህም ኡጋንዳ እና ኬንያን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እንዲሁም ቀጣናዊ ውህደትን እና የጋራ እድገትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል ሩቶ በንግግራቸው፡፡
ከዊሊያም ሩቶ የካምፓላ ጉብኝት አስቀድመው የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከአንድ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ኡጋንዳ የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው÷ የገቢ ንግዷን የምታሳልጠው በኬንያው ሞምባሳ ወደብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኡጋንዳ ብሔራዊ ደህንነት እና የኢኮኖሚ እድገት ያለ ባሕር በር ሊረጋገጥ አይችልም ያሉት ሙሴቪኒ የባሕር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙሲቬኒ በባሕር በር ጉዳይ ላይ ሃሳብ መስጠታቸውን ተከትሎም የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያቸውን በተዛባ መንገድ ማሰራጨታቸው ተመላክቷል፡፡
እንደ ሆርን ሪቪው ዘገባ መገናኛ ብዙሃኑ የፕሬዚዳንቱን ሃሳብ የኡጋንዳ መንግስት በኬንያ የወደብ ኪራይ መክፈል እንደማይፈልግ እና ከኬንያ በሃይል ወደብ እንደሚወስድ አስመስለው መዘገባቸውን አስነብቧል፡፡
በአንጻሩ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በመገናኛ ብዙሃኑ የተሳሳተ መረጃ ሳይወዛገቡ ጉዳዩን በተመለከተ ወደ ካምፓላ በማምራት ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር አዎንታዊ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸው ሀገራቱ በመሰረተ ልማት ትብብር በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ኬንያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ያሳየ መሆኑን ዘገባው አውስቷል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ትብብርም በቀጣይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በጋራ በመገንባት እና በባሕር በር ትብብር ዘርፍ የበለጠ ሊገለጥ ይችላል መባሉን ኦል አፍሪካ ዶት ኮም እና ዴይሊ ሞኒተር ዘግበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ