አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በደረቅ ወደብ ልማትና የሎጅስቲክስ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት በቀጣናው የገቢና ወጪ ምርቶች ዝውውርን ለማቀላጠፍ በትኩረት እየሰራች ነው አሉ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከዲፒ ወርልድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በኩባንያው መካከል ያለውን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና ሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል፡፡
በተለይም በደረቅ ወደብ ልማት፣ በሎጅስቲክስ መሰረተ ልማት ማስፋፋትና ማዘመን እንዲሁም የንግድ ኮሪደሮችን በማስፋት ዙሪያ ከኩባንያው ጋር በጋራ በመስራት በቀጣናው የገቢና ወጪ ምርቶች ዝውውርን ለማቀላጠፍ በትኩረት እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ለቀጣናዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፥ ውጥኑን ከግብ ለማድረስ ከዲፒ ወርልድ ጋር ያላትን አጋርነትና ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የዲፒ ወርልድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም በበኩላቸው፥ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የሚያደርገው ኢንቨስትመንት ዘላቂና ለቀጣናው ማህበረሰብ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በጋራ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በማፋጠን ኢትዮጵያ የቀጣናው የሎጅስቲክስ ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በዲጂታል ሎጅስቲክስ፣ በአቅርቦት ሰንሰለት ዝርጋታ እንዲሁም በነጻ የኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታ ዙሪያ አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመቃኘትና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡