ቢዝነስ

የሆርቲካልቸር ዘርፍ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎች …

By Melaku Gedif

November 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሆርቲካልቸር ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡

በሚኒስቴሩ የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ የሚኒስተር ዴዔታ አማካሪ አሊ መሃመድ (ፕ/ር)÷ በ10 ዓመቱ የግብርና ዘርፍ ዕቅድ በትኩረት ከሚሰራቸው መካከል ሆርቲካልቸር አንዱ ነው፡፡

በተለይም የአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም እና ሌሎች የሆርቲካልቸር ሰብሎች ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአቮካዶ ምርታማነትን ለማሳደግ የ15 ዓመት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት አማካሪው÷ በዚህም ከሜክሲኮ፣ ኬንያ፣ ፔሩና ሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችል ስራ ለመስራት ከፍተኛ በጀት ተመድቧል ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም በኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት ድጋፍ ባለፉት ዓመታት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ሲተገበር የቆየው “ሆርቲ ላይፍ” የተሰኘ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች እና አዳዲስ አሰራሮች የሆርቲካልቸር ዘርፍን ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርምር ስራዎቹ የተሻሻሉ የሆርቲካልቸር ምርት ዝርያዎችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ ያለውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት አጠናክሮ ለማስቀጠልም የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲሰጡ የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የገበያ ትስስርን ለማሳለጥና እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክ ምንዛሪን ለማስፋት እንደሚሰራ ጠቁመው÷ ለዚህም አርሶ አደሩ ምርቱን ያለደላላ ጣልቃ ገብነት በአንድ ማዕከል የሚያቀርብበት ሒደት መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

የሆርቲ ላይፍ ፕሮጀክት ም/ሥራ አስኪያጅ አንድነት ባይለየኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በስድስት የአትክልትና አራት የፍራፍሬ አይነቶች ላይ የተሸሻሉ ዝርያዎችን ከማቅረብ ጀምሮ አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በዚህም የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳድ ከመሬትና ማሳ ዝግጅት ጀምሮ የውሃ፣ የማዳበሪያ፣ የጸረ ተባይና በሌሎች ግብዓቶች አጠቃቀም ዙሪያ የማሳ ላይ ትምህርት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በ11 ወረዳዎች ተጀምሮ አሁን ላይ በ7 ክልሎች በሚገኙ 200 ወረዳዎች በምርምር የተሻሻሉ አሰራሮችን በመከተል ውጤታማ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የተለያዩ ድርጅቶች አዳዲስ ዝርያዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው÷ ለአርሶ አደሮች የብድር ሁኔታ መመቻቸቱንም አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ