አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥራት ላይ በትኩረት መሰራቱ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ እንዲጨምር አድርጓል አሉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ም/ዋና ዳሬክተር ሻፊ ኡመር።
ምክትል ዳይሬክተሩ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በ2017 በጀት ዓመት በቡና ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገብ የተቻለበት ነው።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ እመርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው ÷ ባለፈው በጀት ዓመት 470 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
በእነዚህ ዓመታት በቅንጅት የታገዙ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት አቶ ሻፊ ÷ ባለስልጣኑ ቡና አንዱ የኢኮኖሚ ምሶሶ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በተለይ የቡና ጥራት ተጠብቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር እና የምርት መጠንንም ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በዚህም የተመረጡ የዘር ዓይነቶችን ከመጠቀም ጀምሮ እስከ መጨረሻው ደረጃ ድረስ በባለሙያዎች የታገዘ ድጋፍና ክትትል መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
የቡና ጥራት እንዲጠበቅ ለማድረግ በትኩረት መሰራቱ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት እንዲጨምር ማስቻሉን አብራርተዋል።
በቡና ዘርፍ የተገኘውን ስኬት ለማጠናከር በቡና ምርት ሒደቶች ላይ የተሳተፉ አካላትን በሙሉ የማበረታታትና ለቀጣይም የተሻለ ሥራ እንዲያከናውኑ የመደገፍ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማሕበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በ2017 በጀት ዓመት ከቡና ተከላ ጀምሮ እስከ መላክ ድረስ ባሉት ደረጃዎች በቅንጅት መሰራቱ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ውጤት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ እንደሆነ አንስተው ÷ መንግሥት የሚመለከታቸውን አካላት በማቀናጀት የተረጋጋ ገበያ እንዲኖርና አምራቾችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ማከናወኑን ጠቁመዋል።
ለቀጣይም የቡና ምርትን በብዛት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ ጥራት ላይ በትኩረት በመስራት የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት