የሀገር ውስጥ ዜና

በከባድ የሙስና ወንጀል ምርመራ የተጣራባቸው 11 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል – የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ

By Yonas Getnet

November 27, 2025

‎አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከባድ የሙስና ወንጀል ምርመራ የተጣራባቸው 11 ተጠርጣሪዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ክስ የተመሰረተባቸውም፡- ‎1ኛ ተከሳሽ አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም ጋዎ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረ፤

‎2ኛ ተከሳሽ አቶ ወልደአብ ደምሴ ክብረት በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ግብዓት ምርትና አቅርቦት ዐብይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበረ፣

‎3ኛ ተከሳሽ አቶ ተንሳይ ሜጫ ወ/ስላሴ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ሀብት አመራር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ አባል የነበረ፤

‎4ኛ ተከሳሽ ወ/ሪት መንበረ ኃ/ማርያም ነጋሳ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የኮርፖሬሽኑ የግዢ ኮሚቴ አባል የነበረች፤

‎5ኛ ተከሳሽ አቶ ሚሊዮን ገረመው እሸቱ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የግዢ ባለሙያ እና የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ አባልና ፀሀፊ የነበረ፤

‎6ኛ ተከሳሽ አቶ ሰለሞን ገብሬ መላክ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ፣ የኮርፖሬሽኑ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ አባል፣ የብሄራዊ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ ፀሀፊ የነበረ፤

‎7ኛ ተከሳሽ አቶ መንግስቱ ተስፋ ላቀ በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦት መሪ ሥራ አስፈጻሚ፣ የብሄራዊ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበረ፤

‎8ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ዳኜ ሮሪሳ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የግብዓት ግዢ እና ትራንዚት ክፍል ስራ አስኪያጅ የነበረ፤ ‎ ‎9ኛ ተከሳሽ ካፒቴን ወንድወሰን ካሳ አሰፋ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የነበረ፤

‎10ኛ ተከሳሽ አቶ ጸጋዬ በርሀ ኪዳኑ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበረ፤

‎11ኛ ተከሳሽ አቶ አለባቸው ሞልቶት ዳኜ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የጅቡቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የነበረ

‎በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ‎እነዚህ ተከሳሾች በጋራና በተናጠል የተሰጣቸውን ስልጣን ያለ አግባብ በመጠቀም የክልል መንግስታት ለኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንዲፈፅም የሰጡትን ውክልና እና የኮፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔዎች፣ የግዢ መመሪያዎችን፣ ውሎችና ድንጋጌዎችን በመጣስ ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ተከሳሾቹ የተጋገረውን ማዳበሪያ ማስከስከሻ ወጪ 204 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ያለአግባብ በመክፈል፣ ከመቀሌ መርከብ ጊር ተነቀለ በማለት ኮርፖሬሽኑ 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ የማጓጓዣ ወጪ እንዲያወጣ በማድረግ፤ ጥራት የሌለው ማዳበሪያ የተጓጓዘበት ወጪ 39 ሚሊየን 992 ሺህ 860 የአሜሪካን ዶላርን ጨምሮ በድምሩ 40 ሚሊየን 296 ሺህ 860 የአሜሪካን ዶላር ወይም 5 ቢሊየን 681 ሚሊየን 857 ሺህ 260 በመመዝበር በሕዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዋናነትም በወንጀል አድራጊነት እና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል የምርመራ መዝገብ አጣርቶ በፍትሕ ሚኒስቴር ለዐቃቤ ህግ ከላከ በኋላ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ እንደተመሰረተባቸውም አስታውቋል።

መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ እና በተደረገ ሰፊ ጥናት ‎በአጭር ጊዜ ውስጥ ወንጀሉን አጣርቶ ተከሳሾች ለሕግ እንዲቀርቡ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቀጣይም በከባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ የጀመረውን ክትትልና ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting

Facebook https://web.facebook.com/fanasport

Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!