ጤና

በሲዳማ ክልል የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

By Hailemaryam Tegegn

November 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በክልሉ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አሉ፡፡

የጤና ሚኒስቴር በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የሕክምና ግብዓቶችንና አምስት አምቡላንሶችን ለሲዳማ ክልል አስረክቧል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንዳሉት ፥ በቅርቡ በተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ በሀዋሳ ከተማ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል፡፡

ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በክልሉ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ፥ የጤና ሚኒስቴር በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አድንቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የጤና ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

የበሽታውን ሥርጭት በመግታት ረገድ የክልሉ ሕዝብ ከንክኪ እንዲታቀብና በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎች ሕክምና እንዲደረግላቸው ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።