አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ሂደት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይገባል አሉ የትምህርት ሚኒስትር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75ኛ ዓመት አልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አካል የሆነ የአጋሮች መርሐ ግብር እና ‘ለዘላቂ ልማት እና ለአፍሪካ መጻኢ ዕጣ ፈንታ የከፍተኛ ትምህርት ሚና’ በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ለሀገራት ሁለንተናዊ እድገት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው።
ተቋማቱ የተማረ የሰው ኃይልን በማፍራት እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ሂደት ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የደቡብ ደቡብ ትብብር ምክትል ዋና ፀሐፊ ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ዘላቂ ልማት የሚለካው በእውቀትና በእሴት መጎልበት እንዲሁም በማህበረሰብ ለውጥ ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸው ሚና ቁልፍ መሆኑንም ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘላቂ ልማት ላይ ስርዓተ ትምህርት ቀርፀው መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማህበረሰብ ተኮር ምርምር እና ፈጠራ ላይ የማተኮር ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተመላክቷል።