ቴክ

የሳተላይት መረጃን ያለማቋረጥ የሚቀበል ቴክኖሎጂ ስራ ጀመረ

By sosina alemayehu

December 01, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የሳተላይት መረጃን ያለማቋረጥ የሚቀበል ቴክኖሎጂ ስራ አስጀመረ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ከሳተላይት መረጃን ያለማቋረጥ የሚቀበሉ ቴክኖሎጂዎች ከሚገኙ 10 ማዕከሎች ውስጥ ዘጠኙ ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው ለከተማ ፕላን፣ ለኮንስትራክሽን፣ ትራንስፖርት፣ ግብርና፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ማዕድንና ሌሎች አገልግሎቶች መዘመንና መቀላጠፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ የቴክኖሎጂ ማዕከሎችን በከተሞች ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው÷ ቴክኖሎጂው ወደ ሥራ መግባቱ በከተሞች እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የምናደርገውን ጥረት የሚደግፍ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል አሰራር ለምታደርገው ጉዞ መሰረት ከሆኑ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው ያሉት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ ናቸው።

የሳተላይት መረጃን ያለማቋረጥ የሚቀበለው ቴክኖሎጂ አሁናዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ ከዚህ በፊት በጂፒኤስ በርካታ ቀናት ይፈጅ የነበረውን መረጃ የመሰብሰብ ሥራ በሰዓታትና ደቂቃዎች ውስጥ ማግኘት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ መስፋፋት ከዚህ በፊት ለመነሻ የሚሆነውን መረጃ ለመውሰድ ወደ ማዕከል የሚመጡ አካላት ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑም ተመላክቷል።

በቅድስት አባተ