አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለክልሉ ሰላምና ልማት በጋራ መቆም ይገባል አሉ።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በጋምቤላ ክልል ደረጃ በዲማ ወረዳ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሕገ መንግሥቱ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያጎናፀፈውን መብት በመጠቀም የክልሉን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በዓሉ ሲከበር የሕዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የሚሸረሽሩ እንቅስቃሴዎችን በመታገልና የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነትን በማፅናት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዓሉ አንድነቱን አጠናክሮ በልማቱ እየተጋ ለሚገኘው ሕዝብ አብሮነቱንና ሰላም ወዳድነቱን የሚያሳይበት መድረክ ነው ሲሉም አውስተዋል።
የክልሉ ሕዝብ ያለውን በቂ ሃብት አልምቶ የራሱን እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንዲችል በቅድሚያ የክልሉን ሰላም ዘላቂ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች እንደሚጠናከሩ መረጋገጣቸውንም የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ክልሉ ለጀመራቸው የዘላቂ ሰላምና የልማት ሥራዎች መሳካት ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሯ አመልክተዋል።
የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባዔ መሠረት ማቲዎስ በበኩላቸው÷ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ጎልብቶ እንዲቀጥልና ዴሞክራሲያዊ አሰራሮቻችን እንዲጎለብቱ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።