የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን አየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቅ ዘመናዊ አየር ሃይል ተገንብቷል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

By Melaku Gedif

December 01, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን አየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቅና ዘመኑ የደረሰብትን የውጊያ ስልት የሚመጥን አየር ሃይል ተገንብቷል አሉ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ፡፡

ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክተው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ አየር ሃይል የኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ምልክት ነው ብለዋል፡፡

አየር ሃይል ኢትዮጵያ ከገነባቻቸው ዘመናዊ፣ ስመገናና እና ረጅም ታሪክ ካላቸው ተቋማ ውስጥ አንዱ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

በታሪክ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተከሰቱ አደጋዎችን መስዋዕትነት በመክፈል መቀልበስ የቻለ ተቋም እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በአፍሪካ ሀገራት በሰላም አስከባሪነት በመሰማራት የሕዝቦችን ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና ሰላም ማስከበር መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

ኢትዮጵያ ታፍራ፣ ተከብራና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ አየር ሃይል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ምልክ የሆነው አየር ሃይል የተቃጡ ወረራዎችን ከመቀልበስ አንጻር አይተኬ ሚና መወጣቱን አስታውሰዋል፡፡

አየር ሃይል በኢትዮጵያ የመንግሥታት ለውጥ ሒደት ላይ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን በማለፍ አሁን ላይ መድረሱን አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሊከሰት የሚችልን ጦርነት እንደ ከዚህ ቀደሙ ምሽግ በመቆፈር መመከት አይቻልም፤ ለዚህም ዘመኑን የሚመጥን አየር ሃይል መገንባት ያስፋልጋል ነው ያሉት፡፡

በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ የሶስት ሀገራት አየር ሃይል ተርታ ለመሰለፍ እቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ዘመኑን የዋጀ፣ በሥነ ልቦና የታነጸ፣ ከፖለቲካ እና ብሔርተኝነት ነጻ የሆነ የሰው ሃይል ከማፍራት አንጻር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ቴክኖሎጂው የደረሰበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትም አስፈላጊ ትጥቆችን የማሟላትና መሰረት ልማቶችን የመገንባት ሥራ እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ