ቢዝነስ

የኢንቨስትመንት ፍሰትን ያሳደገው የባለሃብቶች ጥያቄ ምላሽ ማግኘት

By Adimasu Aragawu

December 02, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በባለሃብቶች ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ መሰጠቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስችሏል አለ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ምላሽ ካገኙት ጥያቄዎች መካከል 14 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መቀየር ይገኝበታል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዘው ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሠረት ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻዎችን ማስፋቱ ድርጅቶች በቀላሉ ምርታቸውን ወደ ተለያዩ ሀገራት እንዲልኩ ማስቻሉ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ የጎላ ሚና አበርክቷል ብለዋል።

በኮሚሽኑ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን፣ ግልጽና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መሰጠቱ አስተዋጽኦ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአጠቃላይ በዘርፉ በተደረጉ ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ሥራዎች በፈረንጆቹ 2024/25 ከአራት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንደተመዘገበ አረጋግጠዋል።

ኢንቨስትመንት በይበልጥ እንዲስፋፋና እንዲነቃቃ ኮሚሽኑ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማስተዋወቅ የሚያስችል የአምስት ዓመት የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ በማውጣት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።

ቀደም ሲል የነበረውን ስትራቴጂ ወደ ኢላማ ተኮር የኢንቨስትመት ማስተዋወቅ ሥራ በመቀየር ከሌሎች ተቋማት ተግባራት ጋር በቅንጅት እየተሠራበት እንደሚገኝም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!