የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የሹመት ደብዳቤያቸውን ለተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት አቀረቡ

By Adimasu Aragawu

December 02, 2025

‎አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የሹመት ደብዳቤያቸውን ለተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አቀረቡ።

በዛሬው ዕለት በቃስር አል ዋታን ቤተ መንግሥት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የሹመት ደብዳቤያቸው ለፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከውን ወንድማዊ ሠላምታ እና መልካም ምኞት መልዕክት አድርሰዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ለ54ኛ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የምስረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ በማለት ለፕሬዚዳንቱና ለመላው የሀገሪቱ ህዝብ ልባዊ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሎጂስቲክስና በመሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ወደ አዲስ ከፍታ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ከተባበሩት ዐረብ ኤሜሬቶች ባለስልጣናት ጋር በቅርበት በመስራት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቃል መግባታቸውን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን የተቀበሉት ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለአምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው በመመኘት÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ወዳጅነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ልማት፣ ብልጽግና እንዲሁም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!