የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት በማሳለጥ የጎላ ሚና አለው – አቶ አህመድ ሺዴ

By Adimasu Aragawu

December 02, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት በማሳለጥ የጎላ ሚና አለው አሉ፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።

አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን መፃኢ የፋይናንስ ሥርዓት የሚያሳልጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

ማሻሻያው ወደ ተሟላ ትግበራ ከገባ ወዲህ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማረጋገጥ በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገር ውስጥ ገቢን በማስፋት እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል።

በኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሰረት ወደ ሥራ የገባው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት በማሳለጥ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ሪፎርም መደረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድግ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

ሪፎርሙ ግልጽነትን በመፍጠር፣ በማዕከላዊ ባንክ ላይ ብቻ የተመሰረተውን የፋይናንስ ሥርዓት በመቀነስ እና የታክስ መሰረቱን በማስፋት የሚታይ ለውጥ ማምጣቱን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተዓማኒና ለግሉ ዘርፍ ተስማሚ የፋይናንስ ምህዳር ለማስፈን በተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን መሰረተ ልማት በተለያዩ የቦንድ ኢንቨስትመንት አማካይነት ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!