አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለወራት ተቋርጦ የቆየው የሲቲ ስካን አገልግሎት ዳግም ጀምሯል።
በሆስፒታሉ ከወራት በፊት በስቲ ስካንና ኤም አር አይ የህክምና መሳሪያዎች ታግዞ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መዘገቡ ይታወሳል።
በወቅቱ የአካባቢው ታካሚዎች በሁለቱ መሳሪያዎች ሲያገኙት የነበረው አገልግሎት በመቋረጡ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተሞች አገልግሎቱን ሲያገኙ ቆይተዋል።
ታካሚዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ በመሳሪዎቹ ሲያገኙት የነበረው ህክምና ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ለተለያዩ እንግልቶች ሲዳርጋቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ታካሚዎች ላቀረቡት ቅሬታ የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል በሰጠው ምላሽ የተበላሹ ማሽኖችን አስጠግኖ ወደ ስራ ለመመለስ የጨረታ ሂደት ላይ እንደነበር መግለፁ ይታወሳል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ትምህርትና ህክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ ደምስ ሙላቱ እንዳሉት÷ በተቋሙ የሲቲ ስካንና ኤም አር አይ አገልግሎት በብልሽት ምክንያት ለወራት በሆስፒታሉ ተቋርጦ ነበር።
ዩኒቨርሲቲው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው÷ በ17 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የተበላሸው ሲቲ ሲካን ማሽን ሙሉ በሙሉ ተጠግኖ ለታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።
በዚህም በታካሚዎች ላይ ተፈጥሮ የነበረው እንግልት አሁን ላይ መፈታቱን አስረድተዋል።
ኤም አርአይ ማሽኑ ወደ ስራ እንዲመለስ የተደረገው ጥረት እስካሁን አለመጠናቀቁንና ይህንንም ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
በሆስፒታሉ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሌላ አካባቢ ይጓዙ እንደነበር የሚናገሩት ተገልጋዮች÷ ሲቲ ስካኑ ስራ በመጀመሩ በቅርበት የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
በምናለ አየነው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!