የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ኢነርጂ ኤፊሸንሲ ጉባዔ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

By abel neway

December 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመጀመሪያው የአፍሪካ ኢነርጂ ኤፊሸንሲ ጉባኤ ከፊታችን ታሕሳስ 1 እስከ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።

የአፍሪካ ኢነርጂና መሰረተ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌራቶ ማታ በሰጡት መግለጫ ÷ የኃይል አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ የኢነርጂ አጠቃቀም ላይ በትኩረት መስራት ይገባል።

የአህጉሪቱ ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት ግብዓት በሆነው የኢነርጂ አጠቃቀም ላይ በትኩረት መምከር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በአህጉሪቱ ያለውን እምቅ የኃይል ሃብት በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው ÷ ለዚህም ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በአቅርቦትና ጥራት ላይ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ኢነርጂ ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ሌራቶ ማታ ÷ ዘርፉ አሁን ላይ አህጉራዊ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ አብራርተዋል።

በጉባዔው የአፍሪካ ሀገራት ኢነርጂ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ600 በላይ እንግዶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በወንድማገኝ ጸጋዬ