አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው አርቲ የሚዲያ ተቋም ያዘጋጀው የአፍሪካ ሚዲያ የዕውቅና መርሐ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በዕውቅና መድረኩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትአለም መለሰን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት የኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ዘርፍ ሚኒስትሮችና ተወካዮች እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የፓን አፍሪካኒስት የቀድሞ መሪዎች ልጆች እንዲሁም በአህጉሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ታድመዋል።
የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት በጋዜጠኝነት፣ በብሮድካስቲንግ፣ በዲጂታል ሚዲያ እና በትርክት ግንባታ የአፍሪካ ስኬቶችን ያሳዩ የሚዲያ ተወካዮች የሚሳተፉበት ነው።
ከ40 ሀገራት የተወጣጡና በተለያዩ ዘርፎች በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩ ከ800 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል 21ዱ እጩዎች በተለያዩ ምድቦች ዛሬ ለፍጻሜ ደርሰዋል።
የአፍሪካን ሰላም፣ ልማትና ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስራዎች የሽልማቱ አካል ሲሆኑ፥ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የሚታወቁ ግለሰቦችና ተቋማትም በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ብሮድካስቲንግ፣ የፓትሪስ ሉሙምባ ፋውንዴሽን፣ የክዋሜ ንክሩማህ ፋውንዴሽን፣ የምዋሊሙ ኒዬሬሬ ፋውንዴሽን፣ የኬኔት ካውንዳ ሌጋሲ ፋውንዴሽን፣ የሲሱሉ ፋውንዴሽን ለማኅበራዊ ፍትህ፣ የፒኤልኦ ሉሙምባ ፋውንዴሽንና የሩስያው አር ቲ ሚዲያ የሁነቱ ቀዳሚ አጋር መሆናቸው ነው የተገለጸው።
በአሸናፊ ሽብሩ