አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በውድድር ዓመቱ ደካማ እንቅስቃሴ እያሳየ በሚገኘው ሊቨርፑል በግሉ የተሻለ ብቃት በማሳየት እያንጸባረቀ የሚገኘው ዶሚኒክ ሶቦዝላይ፡፡
በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመራው የመርሲሳይዱ ክለብ በሁሉም ውድድሮች አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፈ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ሊቨርፑል ወጥ ብቃት ማሳየት ተስኖት ፈታኝ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ቢገኝም ዶሚኒክ ሶቦዝላይ ግን ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል፡፡
በሊጉ ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ በተጋጣሚዎቹ ተደጋጋሚ ሽንፈት እየገጠመው በሚገኘው ሊቨርፑል ውስጥ ሶቦዝላይ በየጨዋታው ታታሪነቱን እያስመለከተ ነው፡፡
በአማካይና በቀኝ የተከላካይ መስመር ለቡድኑ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘው ተጫዋቹ ወጥ ብቃት ማሳየት በተሳነው ሊቨርፑል በልዩነት እያንጸባረቀ ይገኛል፡፡
በሜዳው አንፊልድ ሮድ ሳይቀር በተለያዩ ቡድኖች በሚሸነፈውና ነጥብ በሚጥለው ቡድን ውስጥ ብቻውን ቡድኑን ለማዳን የሚያደርገው ተጋድሎ የሚያስደንቅ ነው፡፡
ዶሚኒክ ሶቦዝላይ በዚህ የውድድር ዘመን እያሳየ ባለው ምርጥ እንቅስቃሴ በዓለም እግር ኳስ ቤተሰብ እየተሞካሸ ይገኛል፡፡
ከትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ መልቀቅ በኋላ በቀኝ ተመላላሽ የተከላካይ ስፍራና የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ሊቨርፑል በዚህ የውድድር ዘመን እየተቸገረ መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው፡፡
ሶቦዝላይ ከመሃል ሜዳ ሚናው በተጨማሪ ይህንን የቀኝ ተመላላሽ የተከላካይ ስፍራ ክፍተትን በመሙላት በመስመር ላይ የሚደረገውን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቀሴ በማገዝ ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
በዚያ መስመር በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚሰለፈው ሞሃመድ ሳላህ የመከላከል ስራው ላይ ደካማ በመሆኑ ሶቦዝላይ ያንን ክፍተት በመሸፈን የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
ቡድኑ በተሸነፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ሜዳውን በሙሉ እያካለለ የሚጫወት ድንቅ ብቃት ያለው ተጫዋች መሆኑን በተደጋጋሚ እያሳየ ይገኛል፡፡
የሊቨርፑል የልብ ምት መሆን የቻለው ሶቦዝላይ ከእሱ የሚነሱ ኳሶች ለሊቨርፑል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው እያሳየ ነው፡፡
25 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ዶሚኒክ ሶቦዝላይ ከኳስ ጋር ካለው ንክኪ በተጨማሪ ቡድን የሚመራበት አሰደናቂ ችሎታውም እያስወደሰው ይገኛል፡፡
በዚህ የውድድር ዘመን ሊቨርፑል አርሰናልን በሊጉ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ በግሩም ሁኔታ በቅጣት ምት ማስቆጠሩ አይዘነጋም፡፡
ሶቦዝላይ ያስቆጠራት የቅጣት ምት ግብ ከውድድር ዓመቱ ምርጥ ጎሎች መካከል አንዷ ስለመሆኗ በብዙ የስፖርት ተንታኞች ተገልጻለች፡፡
በ70 ሚሊየን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ የሊቨርፑል የምን ጊዜም 4ኛ ውዱ ፈራሚ በመሆን አንፊልድ የደረሰው ሶቦዝላይ አሁን ላይ የዝውውር ሂሳቡ 85 ሚሊየን ዩሮ ደርሷል፡፡
3ኛ የውድድር ዘመኑን በሊቨርፑል እያሳለፈ የሚገኘው ሶቦዝላይ በ2024/25 ከሊቨርፑል ጋር የሊጉን ዋንጫ ማሳካት የቻለ ሲሆን እስከ 2028 ድረስ የሚያቆይ ኮንትራት በክለቡ አለው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!